ኢተምድ ከደንበኞች ጋር የጋራ መድረክ አካሄደ፡፡
ሐምሌ 09 ቀን 2018ዓ.ም
አዲስ አበባ (ኢተምድ)
==================
የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት (ኢተምድ) የአገልግሎት አሰጣጡን ይበልጥ ቀልጣፋ ለማድረግና ኢተምድ የጨመራቸው አዳዲስ አገልግሎቶች ለማስተዋወቅ እንዲሁም ከደንበኞቹ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ የደንበኞች የጋራ መድረክ አካሄደ። በመድረኩም የአገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ ለማዘመንና በቀጣዩ የ2019 በጀት ዓመት ጥራቱን የጠበቀና ፈጣን አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችሉ ውይይቶች ተደርገዋል።
የኢተምድ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ኢንጂነር መዓዛ አበራ መድረኩን በንግግር የከፈቱ ሲሆን፣ ተቋሙ በ2018 በጀት ዓመት የአገልግሎት ወሰኖችን ለማስፋትና ዓለም አቀፍ አሰራርን የተከተሉ የጥራት ማረጋገጫዎችን ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል። ይህ የጋራ መድረክም በጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት ሂደት ወቅት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታትና በቀጣዩ ዓመት የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያለመ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በመድረኩም ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ዋና መ/ቤት ብቻ ተወስነው የነበሩ የፍተሻ አገልግሎቶችን በአዳማና በድሬዳዋ ላብራቶሪዎች በማደራጀት ወደ ክልል ቅርንጫፎች የማስፋት ሥራ መከናወኑና በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተገለጸ ሲሆን፣ በመድረኩም ስለ አጠቃላይ አሰራሩና አዳዲስ የአገልግሎት ወሰኖች ማብራሪያ ተሰጥተዋል። የመድረኩ ተሳታፊዎችም በዘመናዊ የፍተሻ መሣሪያዎች የተደራጀውን የኢተምድን የምግብና መጠጥ ፍተሻ ላብራቶሪ በአካል ጎብኝተዋል።
በመጨረሻም የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ኢንጂነር መዓዛ አበራ ውይይቱ ፍሬያማ እንደነበር በመግለጽ፣ ለጥራት ተቋም የደንበኞች ግብዓት ወሳኝ በመሆኑ የተነሱት ጠቃሚ ሃሳቦች በቀጣይ ሥራ ላይ እንደሚውሉ አረጋግጠዋል።






Related Posts
«በጥራት እንሻገር» በሚል መሪ ቃል የጥራት የውይይት መድረክ ተካሄደ፡፡
ኢተምድ በወላይታ ዞን አረካ ከተማ የክረምት በጎ አድራጎት አገልግሎት መርሃ- ግብር አካሄደ።
የውሃ መሠረተ- ልማት ግብአቶችን ጥራት ለማረጋገጥ የሚያስችል የምክክር መድረክ ተካሄደ፡፡