ኢተምድ እና ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በጥራትና ምርምር ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት ተስማሙ

ኢተምድ እና ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በጥራትና ምርምር ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት ተስማሙ፡፡
ሚያዝያ 29 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ (ኢተምድ)
==================
የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት(ኢተምድ) እና የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ። ስምምነቱ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በአገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች የሚገኙ የሀገር ሃብቶችን በጋራ ለመጠቀም እና ጠንካራ የሥራ ትብብር በመፍጠር የምርቶችና አገልግሎቶች ጥራት እና ሳይንሳዊ ምርምር ላይ በጋራ በመስራት ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት ያለመ ነው።
ስምምነቱ የአቅም ግንባታ፣ ምርምርና ልማት፣ የምርቶችና የአገልግሎቶችን ጥራትና ደረጃ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ በጋራ መስራት እና የጥራት ማረጋገጫ ተግባራት ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱን የኢተምድ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ኢንጂነር መዓዛ አበራ እና የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስና ስነ-ቀመር ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ስለሺ ደሜ ዩኒቨርሲቲውን በመወከል ተፈራርመዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ክብርት ኢንጂነር መዓዛ አበራ ለዩኒቨርሲቲው ልዑካን የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የጥራት መንደር ውስጥ የሚገኙ የጥራት መሰረተ-ልማት ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎትና የኢተምድን ሁለንተናዊ የሥራ እንቅስቃሴ የሚዳስስ ገለጻ አድርገዋል። ከስምምነቱ በኋላ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስና ስነ-ቀመር ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ስለሺ ደሜ እና የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በኢተምድ ውስጥ የሚገኙ ዘመናዊ የላቦራቶሪ ፍተሻ የሥራ እንቅስቃሴውን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።