ኢተምድ ለኤም ኬ ዲጂታል ሴኩሪቲ ሶሉሽንስ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት ሰርተፊኬት ሰጠ፡፡

ኢተምድ ለኤም ኬ ዲጂታል ሴኩሪቲ ሶሉሽንስ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት ሰርተፊኬት ሰጠ፡፡
ሐምሌ 01 ቀን 2017ዓ.ም
አዲስ አበባ (ኢተምድ)
==================
የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ለMK Digital Security Solutions PLC ISO 9001 የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት ሰርተፊኬት ሰጠ፡፡ ድርጅቱ ለጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት የተቀመጡ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን ማሟላቱን በተከናወነለት የኦዲት ሂደት ተገምግሞ ብቁ ሆኖ በመገኘቱ ሰርቲፊኬቱን ሊያገኝ ችሏል።
በሰርቲፊኬት ርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ኢንጂነር መዓዛ አበራ የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የእንኳን ደስያላችሁ መልእክት በማስተላለፍ ኢተምድ የሚሰጣቸውን የተስማሚነት ምዘና አገልግሎቶች በተመለከተ ገለፃ አድርገውላቸዋል፡፡ እንዲሁም በሌሎች የተስማሚነት ምዘና የሥራ መስኮች በጋራ ለመስራት የኢተምድን ዝግጁነት ገልፀውላቸዋል፡፡ የኤም ኬ ዲጂታል ሴኩሪቲ ሶሉሽንስ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ይድነቃቸው በቀለ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት የሀገሪቱን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ግብ ለመደገፍና በዘርፉ ተወዳዳሪ ለመሆን ድርጅታቸው ይህንን የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት መተግበሩ በጣም አስፈላጊና ጊዜው የሚጠይቀው መሆኑን ጠቅሰው ሌሎች የሥራ አመራር ሥርዓት ዘርፎችን በተቀናጀ ሁኔታ ለመተግበር የድርጅታቸው ፍላጎት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ሰርቲፊኬቱን የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር መዓዛ አበራ ለድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ይድነቃቸው በቀለ አስረክበዋል፡፡ MK Digital Security Solutions PLC የስማርት ካርድ ህትመት ፋብሪካ ሲሆን ድርጅቱ እንደ ATM card, Sim card, digital ID card ላሉ አገልግሎቶች የሚውሉ እና ሌሎች ካርዶች ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ ሥራዎች ላይ የተሰማራ ድርጅት ነው፡፡