የጤና ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች የጥራት መንደርን ጎበኙ።

በጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ የተመራ የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ አመራሮች እና የተጠሪ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች የተገኙበት የልኡካን ቡድን በዘመናዊ የፍተሻ ቴክኖሎጂዎችና ባለሙያዎች የተደራጀውን የጥራት መንደር ጎበኙ፡፡ በጉብኝታቸው ጥራትን የሚያረጋግጡ ዘመናዊ የፍተሻ መሳሪያዎች የታጠቁ የላብራቶሪና የቢሮ ግንባታ የያዘ እና በብቁ ባለሙያዎች የተደራጀውን የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት የፍተሻ ላብራቶሪዎች ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን የኢተምድ ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር መዓዛ አበራ በተለይም በጥራት መንደሩ የሚገኙ ተቋማት በጤናው ዘርፍ አገልግሎት ላይ የሚውሉ ግብዓቶችና የተለያዩ ምርቶችን ጥራት ከማረጋገጥ አንፃር ኢተምድ እየሰጣቸው ስለሚገኘው አገልግሎቶች ገለፃና ማብራሪያ አድርገውላቸዋል፡፡