የዓለም የጥራት ቀን በኢትዮጵያ ለ13ኛ ጊዜ ከህዳር 26 ቀን – ህዳር 28/ 2016 ዓ.ም “ጥራት፡ መስፈርቶችን ከማሟላት ወደ ላቀ የአፈጻጸም ብቃት” በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት የምርት ጥራት እና የሥራ አመራር ሥርዓት ማረጋገጫ ያገኙ ድርጅቶች በተሳተፉበት ኤግዚቢሽን እና በፓናል ውይይት ተከብሯል፡፡ ኤግዚቢሽኑን ክቡር አቶ እንዳለው መኮንን በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚ/ር የጥራት መሰረተ ልማትና ማረጋገጫ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መርቀው ከፍተውታል፡፡
የዓለም የጥራት ቀን የምርቶችና አገልግሎቶች ጥራት በድርጅቶች ስኬታማነትና በሀገር እድገትና ብልፅግና ላይ የሚጫወተውን የላቀ ሚና ለማስገንዘብ የሚከበር ዓለም አቀፍ ሁነት ነው፡፡ በዚህ በዓል በተስማሚነት ምዘና ድርጅት የጥራት ማረጋገጫ ያገኙ ድርጅቶች የተሳተፉበትና ለህብረተሰቡ ለሶስት ቀናት ክፍት የተደረገው የኤግዚቢሽን ፕሮግራም ህብረተሰቡ ጥራት ያለውን ምርትና አገልግሎት ለይቶ እንዲያውቅ ያስቻለ ነበር፡፡ በተጨማሪም የድርጅቱን ላቦራቶሪዎች ለጉብኝት ክፍት በማድረግ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲጎበኙትና ድርጅቱ እየሰጣቸው የሚገኙ አገልግሎቶችን በተመለከተ ግንዛቤን ማስጨበጥ ተችሏል፡፡ እንዲሁም የምግብና መጠጥ ጥራትና ደህንነት እና በግንባታ እቃዎችና ኮንስትራክሽን ጥራትና ደህንነት ዙሪያ የተለያዩ አምራቾችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የፓናል ውይይትም ተደርጓል።
በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ላይም በበዓሉ ተሳታፊ ለነበሩት ድርጅቶች ላደረጉት ተሳትፎ የምስጋና እና የእውቅና የምስክር ወረቀት ከድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መዓዛ አበራ እጅ ተበርክቶላቸዋል፡፡
Related Posts
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዝዳንት ክቡር ታዬ አጽቀ ስላሴ የጥራት መንደርን ጎበኙ።
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አመራሮችና ሠራተኞች የጥራት ኤግዚቢሽንንና የኢተምድን ላብራቶሪዎች ጎበኙ
የተለያዩ የመንግስት ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች፣አምራች ድርጅቶች እና የተለያዩ ማህበራት የጥራት መንደርን ጎበኙ።