የኢተምድ ዋና ዳይሬክተር የድሬዳዋ ነጻ ንግድ ቀጠናን ጎበኙ፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ክቡር ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መአዛ አበራ የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠናን የመስክ ጉብኝትና ውይይት አካሂደዋል፡፡
በጉብኝቱና ውይይቱ ወቅት ኢተምድ በነፃ ቀጠናው ላይ ቢሮ በመክፈት አገልግሎቶች በቅርበት እንዲሰጥ ከስምምነት ተደርሷል፡፡ በዚሁ መሰረትም የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት በድሬዳዋ ከተማ ቅ/ፅ/ቤት በመክፈት የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት እየሰጠ የቆየ ቢሆንም አሁን በነፃ የንግድ ቀጠናው ካለው የአገልግሎት ፍላጎት አንፃር በሚቀጥሉት አጭር ጊዜያት ውስጥ ተጨማሪ ፅ/ቤት በነፃ የንግድ ቀጠናው ከፍቶ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አበራ በውይይቱና በጉብኝቱ ወቅት ለሥራ ኃላፊዎቹ አረጋግጠውላቸዋል፡፡
በተጨማሪም ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አበራ ከድሬዳዋ ደረቅ ወደብ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በደረቅ ወደቡ በመገኘት ውይይትና የመስክ ጉብኝት ያካሄዱ ሲሆን የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት በደረቅ ወደቡም ፅ/ቤት በመክፈት የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ገልፀውላቸዋል፡፡