የገንዘብ የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ዴኤታ ኢተምድን ጎበኙ

ክብርት ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው የገንዘብ የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ዴኤታ በኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት (ኢተምድ) በመገኘት በዓለም ባንክ ፕሮጀክት የተሰሩ የላብራቶር የአቅም ግንባታ ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡ በጉብኝታቸው ዓለም በደረሰበት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች መሰረት የተደራጁ ዘጠኝ የፍተሻ ላብራቶሮችን እና አጠቃላይ የድርጅቱን አገልግሎት የመስጠት አቅም እንዲጎበኙ ተደርጓል፡፡

ከጉብኝታቸው በኃላ እንደገለጹት ኢተምድ እየሰጣቸው የሚገኙ የምርት ጥራት ፍተሻ አገልግሎቶችን በአካል ተገኝተው ማየት በመቻላቸው መደስታቸውን ገልፀው፤ ለሀገር ውስጥ  እና ለዓለም ገበያ የሚቀርቡ የተለያዩ የምርት አይነቶችን ጥራት ለመፈተሽ የሚያስችል ብቁና ዘመናዊ ላብራቶር እንዳለን ለመረዳት አስችሎኛል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርቶች በውጪ ሀገራት ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል እና ወደሀገር የሚገቡ ምርቶችም ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ መንግስት የተለያዩ ድጋፎችንና የአቅም ግንባታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ዘርፉን ለማጠናከር እንደሀገር ያሉንን ላብራቶሮች አቅም አቀናጅተን በጋራ መስራት አስፈላጊ መሆኑን መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡