የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊዎች ኢተምድን ጎበኙ

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊዎች ኢተምድን ጎበኙ፡፡

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል የተመሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት (ኢተምድ) የስራ ጉብኝት አካሂደዋል፡፡ የጉብኝቱ ዓላማ የምርቶችንና አገልግሎቶች ጥራትን ከማስጠበቅ አንፃር የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተልእኮዎችን ከማስፈጸም አንፃር ያለውን አቅም በአካል ተገኝተው በመጎብኘት በጋራ ለመስራት የሚያስችል ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ያለመ ነበር፡፡

በጉብኝቱ ወቅት የኢተምድ ዘጠኝ የፍተሻ ላብራቶሮች፣ የኢንስፔክሽንና የሰርቲፊኬሽን የአሰራር ስርዓቶች እና አገልግሎት የመስጠት አቅሙ በኢተምድ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መአዛ አበራ እና በኦፕሬሽን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ አቤል አንበርብር ገለፃ ተደርጎላቸዋል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ከጉብኝቱ በኃላ ኢተምድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቃቱን በማረጋገጥ የምርቶችና አገልግሎቶች የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት የመስጠት አቅሙ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድትሆን የሚያስችል ቁመና  ያለው ድርጅት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በመጨረሻም ሚኒስቴር መ/ቤቱና ኢተምድ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ጉብኝት ማድረጋቸውን አረጋግጠዋል፡፡