ኢተምድ የ2014 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀሙን ገመገመ፡፡

             ኢተምድ 2014 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀሙን ገመገመ፡፡

የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት በ2014 በጀት ዓመት አመታዊ እቅድ አፈፃፀሙ 18‚015 የአገልግሎት ጥያቄዎችን በማስተናገድ የምርት ጥራት የላብራቶር ፍተሻ፣ የወጪና ገቢ ምርት ኢንስፔክሽን እና የሰርተፍኬሽን አገልግሎቶችን በመስጠት ጥራት ያለው ምርትና አገልግሎት እንዲኖር እና ፍትሃዊ የግብይት ስርዓት እንዲሰፍን ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፡፡ እነዚህም አገልግሎቶች ለ13‚485 የምርት ናሙናዎች የላብራቶር ፍተሻ አገልግሎት፣ለ3‚756 ገቢ እና ወጪ የምርት ናሙናዎች እና 1,694,515.05ሜ/ቶን የግብርና፣ የኢንዱስትሪ ምርቶችና ግብዓቶች የኢንስፔክሽን አገልግሎት እና ለ774 አዲስና ነባር ደንበኞች የሰርተፍኬሽን አገልግሎቶች ሰጥቷል፡፡

ሐምሌ 19ቀን 2014ዓ.ም ኢተምድ ከስራ አመራር ቦርዱ ጋር ባደረገው አመታዊ እቅድ አፈፃፀም የጋራ ግምገማ መድረክ አመታዊ አፈፃፀሙ ከ95% በላይ መሆኑ የሚደነቅ እና ተቋሙ ለቀጣይ ሞዴል የተስማሚነት ምዘና አገልግሎት ሰጪ ተቋም ሆኖ መቀጠል የሚያስችለው መሆኑን ተገልፆል፡፡ በተጨማሪም በግምገማው የቦርዱ ሥራ አመራር አባላት ለ2015 በጀት ዓመት ድርጅቱ የመወዳደር አቅሙን በማሳደግና አገልግሎቱን በስፋት በማስተዋወቅና በመሸጥ ስራውን በማጠናከር ከባለድርሻ አካላት በተለይ ከተቆጣጣሪ መ/ቤቶች ጋር በቅንጅት ለውጤት በጋራ የመስራት አስፈላጊነትን አስምረውበታል፤ በተጨማሪም የዓለም አቀፍ ገዥዎች የሶስተኛ ወገን የተስማሚነት ምዘና አገልግሎት ፍላጎትን መሰረት ያደረገ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ዝግጁነት እንደሚያስፈልግ እና ከዓለም አቀፍ መሰል ተቋማት ጋር ተወዳድሮ ተመራጭና ተቀባይነት ያለው ተቋም መሆኑን ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡ ከምርቶችና አገልግሎቶች ጥራት ጋር በተያያዘም የዜጎችን ጤንነትና ደህንነት ከስጋት ነፃ ለማድረግ፣ የአገር ሃብት ሊደርስበት ከሚችለው የምጣኔ ሃብት ብክነት ለመከላከል፣ህጋዊ የሆነ ወጥነት ያለው የአመራረት ሂደት በመከተል በአምራች ኢንዱስትሪውና በተጠቃሚው ማህበረሰብ መካከል እንደ መግባቢያ ቋንቋ በመሆን ማገልገል ከምንግዜውም በበለጠ ጊዜው የሚጠይቀው በመሆኑ ይህንን በተግባር ማሳየት አስፈላጊ እንደሆነ በግምገማው ወቅት ተገልፆል፡፡

  በመጨረሻም የኢፌዲሪ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዲኤታ እና የድርጅቱ ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ እንዳለው መኮንን እንደገለጹት ኢተምድ ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅሙን በሰለጠነ የሰው ሀይልና በዘመናዊ የፍተሻ መሳሪያዎች እያደራጀ እና እያሳደገ በመምጣት ቀደም ሲል በውጪ ሀገራት በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ይሰሩ የነበሩ የፍተሻ አገልግሎቶችን በሙሉ አቅም በመስጠት የውጪ ምንዛሬ ወጪን ከማዳኑም ባሻገር በሀገር ውስጥ የሚመረቱትንም ሆነ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡትን የተለያዩ የግብርና ምርቶች እና የኢንዱስትሪ ውጤቶች ጥራትን የመፈተሸ ስራን በመስራት የሸማቹ ህብረተሰብ ጤንነትና ደህንነት እንዲጠበቅና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆነው የሀገር ኢኮኖሚን በቀጣይነት እንዲያጎለብቱ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡