ከኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት(ኢግልድ) ልዩ ልዩ የስራ ክፍሎች የተውጣጡ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች በኢተምድ የስራ ጉብኝት አካሂደዋል፡፡ የጉብኝቱ ዓላማ በኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት የምርቶች የጥራት ፍተሻ ሂደትን በአካል ተገኝተው መጎብኘት፣ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችንና ምርቶችን ጥራትን ከማስጠበቅ አንፃር ሁለቱ ድርጅቶች በቀጣይ በጋራ የሚሰሩበትን ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እና እንደ ልማት ድርጅትነታቸው የልምድ ተሞክሮ ልውውጥ ማድረግን ታሳቢ ያደረገ ነበር፡፡ በጉብኝቱ የኢተምድ ላብራቶር ፍተሻ፣ የኢንስፔክሽን፣የሰርቲፊኬሽን አገልግሎቶች አሰጣጥ እና ኢተምድ አዘጋጅቶ ተግባራዊ እያደረገው ባለው የኮርፖሬት ማህበራዊ ሓላፊነት መመሪያን (Corporate Social Responsibility Guideline) በተመለከተ በድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሻለ በልሁ አማካኝነት ገለፃ ተደርጎላቸዋል፡፡ በእለቱ በድርጅቱ ውስጥ የጥራት ፍተሻ የሚከናወንባቸውን 9 ላብራቶሪዎች በመዘዋወር ጎብኝተዋል፡፡
ኢግልድ በብቁ የሰው ሀይልና ቴክኖሎጂ በተደገፈ የአሰራር ስርዓት በመታገዝ እና ጠንካራ የአቅርቦትና ግብይት ሰንሰለት በመፍጠር ጥራታቸውን የጠበቁ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በማልማት፣በማቅረብ እና የተመረጡ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ በማድረግ የሀገሪቱ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ማድረግና ገበያ ማረጋጋትን ተልእኮው በማድረግ የሚሰራ ድርጅት በመሆኑ ይህን ተልእኮውን በብቃት ለመከወን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው የፍተሻ ላቦራቶር፣የኢንስፔክሽንና ሰርቲፊኬሽን የአሰራር ሥርዓቶችን በመተግበር ተዓማኒነት ያለው፣ገለልተኛ፣ውጤታማ፣ተደራሽና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ጥራት ያለው ምርትና አገልግሎት እንዲኖር ከሚሰራው የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ኃላፊዎቹ ገልፀዋል፡፡
Related Posts
ኢተምድ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 6,823 የአገልግሎት ጥያቄዎችን በማስተናገድ የጥራት ማረጋገጥ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡
ኢተምድ ለአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት (ISO 9001:2015) ሰርተፊኬት ሰጠ።
ኢተምድ ለራህመት መሃመድ ዱቄት ፋብሪካ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት (ISO 9001:2015) ሰርተፊኬት ሰጠ።