
ኢተምድ ተማሪዎችን በኢንተርሺፕ እና በስራ ላይ ስልጠና እያበቃ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት በተለያዩ የሳይንስና ኢንጂነሪንግ ቴክኖሎጂ ዘርፎች የሰለጠነ ሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በአጋርነት በመስራት በተለያዩ ጊዜያት ተማሪዎችን በኢንተርሺፕ እና በስራ ላይ ስልጠና ብቁ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡
ሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም የአዲስ አበባ ሳይንሥና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው የእጩ ምሩቃን እና ቀጣሪ ድርጅቶች የስራ አውደ ርእይ አካሂዷል። በአውደ ርእዩ ላይም የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅትን ጨምሮ ከ50 በላይ ድርጅቶች እና ከ1 ሺህ በላይ ተመራቂ ተማሪዎች ተሳትፈውበታል። የአዲስ አበባ ሣይንሥና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ደረጄ እንግዳ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ተመራቂ ተማሪዎች በድርጅቶች የስራ እድል የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እና ተማሪዎች ያሏቸውን የፈጠራ ውጤቶችን ማሳየት አላማው ያደረገ አውደ ርእይ መሆኑን ተናግረዋል። በፕሮግራሙ ላይ በክብር እንግድነት የተጋበዙት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የሳይንስና ምርምር ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር ሰለሞን ቢኖር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ብቁ የሰው ሀይል በማፍራት ሀገሪቱ ወደ ተሻለ የእድገት ጎዳና ለምታደርገው ጉዞ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም መንግሥት ተማሪዎች በተግባር የላቀ እውቀት እንዲኖራቸውና ከኢንዱስትሪዎች ጋር ለማስተሳሰር የተለያዩ መመሪያዎችን በማውጣት በትኩረት እየሠራ መሆኑን አንስተዋል።
Related Posts
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አመራርና ሠራተኞች ኢተምድን ጎበኙ፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት የ9 ወራት እቅድ አፈፃፀም ግምገማ ተካሄደ፡፡
የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢተምድ የመስክ ምልከታ አደረገ፡፡