የምግብ ዘይት እና የሥንዴ ዱቄትን በማእድናትና በቫይታሚን የበለፀጉ እንዲሆኑ የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ የምክክር መድረክ  ተካሄደ

የምግብ ዘይት እና የሥንዴ ዱቄትን በማእድናትና በቫይታሚን የበለፀጉ እንዲሆኑ የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ የምክክር መድረክ  ተካሄደ፡፡

የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ከGain (Global Alliance for Improved Nutrition) ጋር በመተባባር የዘይትእናየሥንዴዱቄትንበማእድናትና በቫይታሚንየበለፀጉበማድረግ ሂደት ላይ ከሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች አዲስ አበባን እና ድሬዳዋን ጨምሮ ከተውጣጡ  የምግብ ዘይትና የስንዴ ዱቄት አምራች ድርጅቶች ጋር  የካቲት 18 /2013 ዓ.ም በካፒታል ሆቴል የግንዛቤ ማስጨበጫ የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡

በእለቱ የምክክር መድረኩን የከፈቱት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሻለ በልሁ ባደረጉት  የመክፈቻ ንግግር የመድረኩ ዋነኛው አላማ የምግብ ዘይትና የስንዴ ዱቄትን በቫይታሚን እና በማእድናት የበለፀጉ እንዲሆኑ ለማድረግ በተጀመረው ሂደት ከአምራቾች ጋር መወያየቱ የጉዳዩ ባለቤቶች በመሆናቸው እና ኃላፊነትም ጭምር ያለባቸው በመሆኑ ሲሆን ምክንያቱን ሲገልፁም በቫይታሚን እና በማእድናት የበለፀጉ ምግቦች በአመጋገብ ጉድለትና በተመጣጣነ ትክክለኛ ንጥረ ምግብ እጥረት ሳቢያ የሚከሰቱትን የጤና እክሎች ለመከላከል ጠቀሜታቸው የጎላ በመሆኑ ይህን መድረክ ማዘጋጀት እንዳስፈለገ ተናግረዋል፡፡

ኢተምድ በምግብ ዘርፍ የሚሰጠው አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የ6ሚሊዮን ዶላር በጀት መድቦ የተለያዩ ዘመናዊ የጥራት መፈተሻ መሳሪያዎችን በማደራጀት ላይ እንደሚገኝ እና የአቅም ግንባታ ስራዎችን በማጠናከር የአምራቾችና አገልግሎት ሰጪዎች የተስማሚነት ምዘና የአገልግሎት ጥያቄን ዓለም አቀፋዊ በሆነ አሰራር ለማስተናገድ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደሆነ ለመድረኩ ገልፀዋል፡፡ የምግብ ዘይት በአብዛኛው ከውጪ የምናስመጣው ምርት በመሆኑ በመንግስት በተያዘው አቅጣጫ በሀገር ውስጥ ምርት እንዲተካ ለማድረግ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ስራ የጀመሩ ትላልቅ የዘይት ፋብሪካዎች እንደሚገኙ ጠቁመው እነዚህ የዘይት ፍብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ማምረት ከጀመሩና የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ካሟሉ በኃላ ወደ ውጪ ቢያንስ ለጎረቤት ሀገራት ምርታቸውን መላክን ታሳቢ የተደረገ ሲሆን ከአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስራ መጀመር ጋር በተያያዘ የአምራቾች አሰራርና የአመራረት ዘዴ ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላ እንዲሆን ስራዎችን በጋራ የመስራት አስፈላጊነትን አሳስበዋል፡፡

በተመሳሳይ ቶም ሀቨርኮርት የጌይን ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር የመድረኩን አስፈላጊነት አስመልክቶ ባስተላለፉት መልእክት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የበርካታ ሀገራት ዜጎች በተለይም በማደግ ላይ የሚገኙት ትክክለኛ ይዘት ያለው ምግብ  እንደማይመገቡ ገልፀው በዚህም ምክንያት ብዙ ሕፃናት፣ሴቶችና ወንዶች ለተለያዩ የጤና መታወኮች እንደሚጋለጡ ጠቁመዋል፤ ደህንነታቸው የተጠበቀ እና አልሚ ምግቦች ለእነዚህ ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ እና ተፈላጊነታቸውን ለመጨመር መንግስት፣ አምራቾች እና የልማት አጋሮች በጋራ የመስራትን አስፈላጊነት በአፅንኦት አስገንዝበዋል፡፡ አልሚ ምግቦችን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ አብዛኛው ህብረተሰብ ለምግብነት የሚጠቀመውን የምግብ አይነት በቫይታሚን እና በማእድናት ማበልፀግ ይገኝበታል፡፡ የምግብ ዘይትና ዱቄትም ከእነዚህ በዓለም ዙሪያ አብዛኛው ህብረተሰብ ለምግብነት ከሚጠቀምባቸው ምግቦች ዋነኞቹ መሆናቸውን በመጥቀስ በዓለም ዙሪያ እና በዚህች ሀገር ውስጥ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የተመጣጠነ ምግብ ሊያገኙ የሚችሉት ምግባቸውን ለማብሰል የሚጠቀሙት የምግብ ዘይት  እንዲሁም የሚበሉት ዳቦ በቫይታሚን እና በማእድናት የበለፀገ ከሆነ ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ለአምራቾች በሰጡት ማሳሰቢያም የአምራቾች ወሳኝ ሚና የመንግስትን የአመጋገብ የማስተካከል አጀንዳ በመደገፍ እንዲሁም የዚህች ሀገር ህፃናት፣ሴቶች እና ወንዶች የአመጋገብ ሁኔታ አሁን ካለው ለወደፊቱ እንዲሻሻል መንግስትን እና የልማት አጋሮችን የመደገፍ ኃላፊነት አለባችሁ ብለዋል፡፡

በምክክር መድረኩም የተስማሚነት ምዘና ሚና በጥራት መሰረተ ልማት መዋቅር፣ የምርት ሰርተፍኬሽን ሂደት፣ በማእድናትና በቫይታሚን የበለፀገ የምግብ ዘይት እና የስንዴ ዱቄት የምርት ሰርተፍኬሽን ስኪም (certification scheme) ምግብን በማእድናት ማበልፀግ ያለውን ፋይዳ የሚያስገነዝቡ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ገለፃ የተደረገ ሲሆን በመጨረሻም በቀረቡት ፅሁፎች ዙሪያ ውይይት ተደርጎ ስራዎችን በተጠናከረ መልኩ በጋራ መስራት አስፈላጊ መሆኑ የመድረኩ ተሳታፊዎች አረጋግጠዋል፡፡