ስለ ተስማሚነት ምዘና የፍተሻ ላቦራቶር ውጤቶች ሊታወቁ የሚገቡ ነጥቦች
በዓለም አቀፍ የንግድ መድረክ በገዢና ሻጭ መካከል መተማመንን መገንባት እጅግ አስቸጋሪና የአንድ ጀምበር ስራ ባይሆንም ሶስተኛ ወገን የፍተሻ ላብራቶር አገልግሎትን ለመጠቀም ትክክለኛና አስተማማኝ ውጤት የሚሰጥ የፍተሻ ላብራቶር ማግኘት ቁልፍ ሚናን ይጫወታል።
ስለሆነም አምራቾች፣ ላኪዎችና አስመጪዎች እንዲሁም አገልግሎት ሰጪና ተቆጣጣሪ አካላት ምርቶቻቸውን ከማስፈተሻቸው በፊት ሊጠይቁት የሚገባቸው መሰረታዊ ጥያቄ ቢኖር የፍተሻ ላብራቶር አገልግሎት ሰጪው አካል ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለውን የላብራቶር ሥራ አመራር ሥርዓት (ISO/IEC 17025 laboratory management system) ይከተላል ወይ የሚል ይሆናል። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት በንግዱ መድረክ መተማመንን ለመፍጠር የሦስተኛ ወገን የጥራት ማረጋገጫን መያዝ ወሳኝ በመሆኑና ISO/IEC 17025ን መተግበር ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነትና ቀጣይነት ያለው የፍተሻ ውጤት እንዲኖር የሚያስችል ከመሆኑም በላይ የደንበኛን ፍላጎት ለማርካትና በውጤቱ እንዲተማመን ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። የተስማሚነት ምዘና ተቋማት የፍተሻ ላቦራቶር የሚከተሉት መሰረታዊ ባህርያት ሊኖራቸው ይገባል:-
አስተማማኝ ግብዓት ማሟላታቸው
የፍተሻ ላብራቶር መሳርያዎች በአግባቡ ፈትሸው ተቀባይነት ያለው ውጤት እንዲሰጡ ከተፈለገ አስፈላጊው የፍተሻ ባለሙያና በደጋፊ የሰው ኃይል መደራጀት ይኖርበታል። እዚህ ላይ ጥንቃቄ ሊወሰድ የሚገባው ጉዳይ ቢኖር የፍተሻ ባለሙያው ወቅቱ ከሚጠይቀው የቴክኖሎጂ ለውጥና ፍላጎት ጋር አብሮ የሚራመድ ብቁ መሆኑን ማረጋገጥ ነው። ይህ ደግሞ ላቦራቶሪው የሚጠቀምባቸውን ዘመናዊ የፍተሻ መሣሪያዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ ያስችላቸዋል።
ነጻና ገለልተኛ የፍተሻ ውጤት መስጠት መቻላቸው
በፍተሻ የሚገኙ ውጤቶች ከተጽእኖ ነጻ በሆነ መልኩ ሊመዘኑና ሊለኩ እንዲሁም በሳይንሳዊ መንገድ ሊተነተኑ ይገባል።
መተማመንን መገንባት እና ማስቀጠል መቻላቸው
የሚፈተሸው የምርት መረጃ፣ መለያ(brand) እንዲሁም የኤሌክትሮኒክ የፍተሻ ውጤት በሚስጥር መያዝ አለበት።
ደረጃዎችንና የተረጋጋጡ የፍተሻ ዘዴዎችን መጠቀማቸው
ስኬታማ የፍተሻ ላብራቶር አገልግሎቶችን ለማከናወን የተረጋገጡ የፍተሻ ዘዴዎችን መጠቀም የግድ ይላል። ለዚህ ደግሞ በዘርፉ የሚወጡ ሳይንሳዊ ጽሁፎችን፣ ደረጃዎችን እንዲሁም ለህትመት የበቁ የፍተሻ ዘዴዎችን አረጋግጦ መጠቀም ለፍተሻ ላብራቶር ውጤቶች ተዓማኒነት ወሳኝ ነው።
ቁርጠኛ የሆነ የስራ አመራር እና ተቋማዊ እሴትን መትከላቸው
የፍተሻ ላብራቶር አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በሥራ አመራር እና በፍተሻ ባለሙያዎች መደራጀት ያለባቸው ሲሆን ከተፅእኖ ነፃ በሆነ መልኩ ኃላፊነታቸው ሊወጡ ይገባል።
በተደጋጋሚ ተመሳሳይ የፍተሻ ውጤት መስጠት መቻላቸው
የፍተሻ ውጤቶች ተመሣሣይ የፍተሻ ዘዴ እስከተጠቀሙ ድረሥ በተለያዩ ጊዜያት በተደጋጋሚ ቢፈተሹም ውጤታቸው ተመሣሣይ መሆን ይኖርበታል። ስለሆነም ዳግም ፍተሻን በማያስቀረት የጊዜን፣ የወጪንና አላስፈላጊ እንግልትን ያስቀራል።
የፍተሻ መሳርያዎች ትክክለኛነት
አስተማማኝ የፍተሻ ውጤት ለማግኘት የመፈተሻና የመለኪያ መሣሪያዎች ትክክለኛነትን ማረጋገጥ መሠረታዊ ጉዳይ ነው። ለዚህ ደግሞ የመፈተሻ መሣሪያዎችን በየወቅቱ ከተቀመጡ መስፈርቶች ጋር መናበባቸውን ማረጋገጥ ተገቢ ሲሆን ሥርዓቱ የዳግም ፍተሻን ያስቀራል።
የሥራ አመራር ሥርዓት መገንባታቸው
ደረጃን፣ መመርያንና ህግጋትን የተከተለ የአሰራር ስርዓትን በፍተሻ ላቦራቶር ውስጥ መትከል ቀጣይነት ላለው መሻሻል ቁልፍ ሚናን ይጫወታል።
(ምንጭ፡ ISO focus July-Aug 2016 edition page 34)
Related Posts
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አመራርና ሠራተኞች ኢተምድን ጎበኙ፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት የ9 ወራት እቅድ አፈፃፀም ግምገማ ተካሄደ፡፡
የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢተምድ የመስክ ምልከታ አደረገ፡፡