የተስማሚነት ምዘና በንግድ መድረክ
አዳዲስ ገበያዎችን ዘልቆ ለመግባት ደረጃዎችን መሰረት ያደገረ የተስማሚነት ምዘና አገልግሎት ወሳኝ ነው። ይህም ምርቶችና አገልግሎቶች ከሀገር ውስጥ ገበያ ባሻገር በዓለም ዓቀፍ ገበያ ተፈላጊነታቸውን እንዲጨምር የማይተካ ሚና ይጫወታል። የፍተሻ ላብራቶር፣ የኢንስፔክሽንና የሰርቲፊኬሽን አገልግሎቶች በጥቅሉ የተስማሚነት ምዘና አገልግሎት የሚባሉ ሲሆን ዓላማውም በገዥና ሻጭ መካከል ለሚፈጠር የንግድ ሂደት ነጻና ገለልተኛ የሦስተኛ ወገን መተማመኛ ሰነድ ሆኖ ያገለግላል። ይህም የመተማመኛ ሰነድ ምርቱ ወይም አገልግሎቱ በተቀመጠው የጥራት መስፈርት መሰረት ተፈትሾና ተረጋግጦ ስለሚሰጥና በዓለም አቀፍ ገበያ እንደመግባቢያ ስለሚያገለግል በሁሉም ቦታና ሀገራት ተቀባይነት እንዲኖረው ያደርጋል። ለምሳሌ፤ ቬትናምን ብንመለከት ምርቶቿ ከራሷ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖራቸው አምራች ድርጅቶቿ በተስማሚነት ምዘና አገልግሎት የአሰራር ስርዓት እንዲያልፉ በማድረጓ ኢኮኖሚያዊ አቅሟን ማጠናከርና በንግዱ መድረክም ተወዳድራ እንድታሸንፍ ምክንያት ሆኗታል። በዚህ የአሰራር ሥርዓት ሀገሪቱም ከዚህ የሚከተሉትን ቁልፍ ጥቅሞች አግኝታለች።
የንግድ ተግዳሮቶቿ ተወግዶላታል
ባለንበት የሰለጠነ ዘመን ሀገራት የዜጎቻቸውን ጤንነት ለመጠበቅ የህግ ማዕቀፍ ማውጣት አስፈልጓቸዋል። ሆኖም የሕግ ማዕቀፉ ለዓለም አቀፍ ንግድ መሰናክል ሊሆን አይገባም። በዚህ ምክንያት ሀገራት የሚያዘጋጁት ቴክኒካል ሪጉሌሽን የዓለም አቀፍ ደረጃዎች ድርጅት (ISO) የሚያወጣቸውን ደረጃዎች መሰረት ያደረገ ሊሆን ይገባል። ይህም በውጤቱ ሀገራት ወደ ውጭ የሚልኳቸው ምርቶች በተመሳሳይ መስፈርት እንዲመዘኑና ተቀባይነት እንዲኖራቸው ያስችላል።
የፍተሻ ውጤቶቿ አመኔታን አግኝቶላታል
የተስማሚነት ምዘና አገልግሎት የምርት፣ የአገልግሎትና የአሰራር ሥርዓት የተቀመጠላቸውን የጥራት መስፈርት ማሟላታቸውን የሚረጋገጥበት ሂደት ሲሆን ይህም ተግባር በኦዲተሮች፣ በላቦራቶሮች፣ በኢንስፔክሽንና በሰርቲፊኬሽን ባለሙያዎች የሚከናወን በመሆኑ አሰራሩን ተዓማኒ ያደርገዋል። በዓለም አቀፍ የንግድ መድረክ እያንዳንዱ የፍተሻ ላቦራቶር ውጤት ከሌላው ሀገር ላቦራቶር ውጤት ጋር በንፅፅር በትክክልና በተመሳሳይ መንገድ መከናወናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው መሳርያ በቀዳሚነት በዓለም አቀፍ ደረጃዎች ድርጅት (ISO) የተዘጋጀውን የላብራቶር የሥራ አመራር የአሰራር ሥርዓትን (ISO/IEC 17025 laboratory management system) በመተግበር ሀገራት ተመሳሳይ የፍተሻና የልኬት ሥርዓት እንዲኖራቸው አስችሏል።
ይህ የአሰራር ሥርዓት በተስማሚነት ምዘና አገልግሎት የሚሰጡ የፍተሻ ላቦራቶር ውጤቶች ተዓማኒና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እንዲሁም በወጪና ገቢ ንግድ ወቅት ሊኖር የሚችለውን የዳግም ፍተሻ ያስቀራል። በተጨማሪም ይህንን የአሠራር ሥርዓት ሀገሮች ከተለያዩ ሀገራዊ ፖሊሲዎቻቸው ጋር በማገናኘታቸው ተቆጣጣሪ አካላት በዚህ ደረጃ ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘትን እንደ ቀዳሚ መስፈርት አድርገውታል። ቬትናምም ይህንኑ ማድረግ በመቻሏ እና አምራች ድርጅቶቿም በዚሁ የአሰራር ስርዓት በማለፋቸው የተስማሚነት ምዘና ተቋሞቿ የሚያወጡት የፍተሻ ውጤት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ከማስቻሉም ባሻገር ተቆጣጣሪ አካላት የተስማሚነት ምዘና ተቋሞቿ ከዓለም አቀፍ ሕግጋት ጋር መናበባቸውን እንዲያረጋግጡ ረድቷታል።
(ምንጭ ISO focus July-Aug 2016 edition page 30)
Related Posts
ኢተምድ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 6,823 የአገልግሎት ጥያቄዎችን በማስተናገድ የጥራት ማረጋገጥ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡
ኢተምድ ለአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት (ISO 9001:2015) ሰርተፊኬት ሰጠ።
ኢተምድ ለራህመት መሃመድ ዱቄት ፋብሪካ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት (ISO 9001:2015) ሰርተፊኬት ሰጠ።