የምግብ ደህንነትና ጥራቱን የማረጋገጥ አስፈላጊነት

የምግብ ደህንነትና ጥራቱን የማረጋገጥ አስፈላጊነት

ነፃ ገበያ የፈጠረው የዓለም የወቅቱ የግብይት ስርዓት የንግድ ልውውጥ ያለ ገደብ እንዲካሄድ ቢፈቅድም በተለይም ኢንዱስትሪ መር በሆኑት ሀገራት የምግብ ደህንነትና ጥራት ከዋጋው በላይ ከፍተኛ ትኩረት እየሰጡት ይገኛሉ፡፡ ይህም የሚያመለክተው ሀገራት ከምርት ብዛት ወደ ምርት ጥራት የአሰራር ሥርአት አምራቾች እንዲቀየሩ አስገዳጅ ሁኔታዎችን እየፈጠሩ መሆኑን ነው፡፡

በዚህ ዘመን የአመራረት ዝንባሌ በዓለም አቀፍ ገበያ ተመራጭና ተወዳዳሪ ሆኖ ለማሸነፍ ከምርቱ ጥራት ባልተናነሰ፣ ምርቱ የሚገኝበት  አካባቢና የሚመረትበት መሣርያ  እንዲሁም መለያው ለተፈላጊነቱ ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ መገኘታቸው  ነው፡፡ ምግብ በሚደጐምባቸው እንዲሁም የላላ የቁጥጥር ስርዓት ባላቸው ሀገራት ሳይቀር ጥራትና ደህንነት በገበያ ለማሸነፍ ወሳኝ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡

በተጨማሪም ከማደግ ጋር ተያይዞ በሚመጣ የፍላጎት መጨመር የተነሳ የምርት ጥራት መስፈርቶች እንዲበራከቱ ምክንያት ሆኗል። የማህበረሰብ ጤናና የአካባቢ ደህንነት የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳዮች በመሆናቸው የምርት ጥራትን ማረጋገጥ የሀገራት ቁልፍ ተግባር እየሆነ መጥቷል።

በተለይ የግብርና ውጤቶችን አስመልክቶ ፍላጐቱ እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ አዳዲስ  መስፈርቶችን ሀገራት በማውጣት የምርት ጥራትንና ደህንነትን ለማረጋገጥ በማያቋርጥ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙ ነው። ይሕም ለአምራቹ፣ በኢንዱስትሪ አቀነባብሮ ወደ ገበያ ለሚያወጣው እንዲሁም የምርቶች ጥራት ላይ ለተሰማራው ባለሙያ እንደ መልካም አጋጣሚ ይቆጠራል፡፡ ለዚህም ሀሳብ እንደ ምሳሌ ለምግብነት የሚውሉ የእንስሳት ተዋፅኦን በተለይ የስጋ ምርቶችን ስናይ የምግቦቹ ጥራትና ደህንነት እንዲረጋገጥ ሀገራት አስገዳጅ የጥራት ቁጥጥር እንዲከተሉ አስገድዷል። ገና ከጅምሩ የቁጥጥር ሥራቸውን በማጠናከር በእርድ ወቅት እና ከእርድ በኃላ በምግብ ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ ጐጂ ተህዋሲያን እንዳይፈጠሩ ልዩ ትኩረት በመስጠት የችግሩን አሳሳቢነት ለመቀነስ ቀጣይነት ያላቸው የቁጥጥር ተግባራት እየፈጸሙ ይገኛሉ፡፡