ኢንቨሰትመንትና የተስማሚነት ምዘና

ኢንቨሰትመንትና የተስማሚነት ምዘና

አንድን ምርት ወይም አገልግሎት ወደ ተጠቃሚ ከመድረሱ በፊት ጥራትና ደህንነቱ በተስማሚነት ምዘና ሥርዓት ማለፍ የግድ ይላል፡፡ ይህም መዋለ ነዋዪን ለሚያፈስ አካል ወጪን ያላግባብ እንዳያወጣ የሚረዳው ብቻ ሳይሆን ምን ያህል ወጪ በምን ያህል ጊዜ  የሚለውንም ይመልሳል፡፡ የምርቶችን የጥራት ደረጃ የማረጋገጥ ተግባራት የሚከውኑ  የተስማሚነት ምዘና ድርጅቶች በመንግስትም ሆነ በግል የሚከናወን ተግባር ሆኖ የዚህን ውጤታማነት የሚያረጋግጡ አካላትም ይኖራሉ፡፡ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ መዋለ ነዋይ ለማፍሰስ ደግሞ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነትና ዕውቅና ያለው የተስማሚነት ምዘና አገልግሎቶችን መጠቀም ወሳኝ ነው፡፡

ይህም ጉዳይ የድርጅቱን ህልውና የሚወስን ይሆናል፡፡ አምራቾች ምርቱን በሚያመርቱበት ፋብሪካ የጥራት ክትትልና ቁጥጥር ቡድን ቢኖራቸውም 3ኛ ወገን የጥራት ማረጋገጫን መያዝ  ለድንበር ተሻጋሪ የንግድ መድረክ ምትክ የሌለው ሚናን ይጫወታል፡፡ ይህንንም ማረጋገጫ መጠቀም ከወጪና ትርፍ አኳያ ሲታይ በጥቂት ወጪ ብዙ ማትረፍ ያስችላል፡፡ ሸማቹ አካል ደግሞ በተስማሚነት ምዘና ጥራቱ የተረጋገጠና ያልተረጋገጠን ምርት ለመለየት የጥራት ማረጋገጫ ሠርተፊኬቶችን ስለሚጠቀም አምራቹ የምርቱን ጥራት በራሱ አቅም ከመፈተሹ ጐን ለጐን በነፃና ገለልተኛ 3ኛ ወገን ማስፈተሹ አሳማኝ ምስክሩ ብቻ ሳይሆን ከአላስፈላጊ  ወጪና ኪሳራም ይታደጋል፡፡

የሚያስገኘውም ጥቅም ዘርፈ ብዙ ሲሆን በዋነኛነት ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳና የምርት ጥራትን ካለመጠበቅ ከሚከሰቱ የማህበረሰብ ጤናና የአካባቢ ደህንነት ችግሮች መታደግ መቻሉ ነው፡፡ ከዚሁ ጐን ለጐን በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያለው የተስማሚነት ምዘና ስራዎችን የሚተገብሩ ተቋማትን ለይቶ አብሮ መስራት ከሀገር ውስጥ የንግድ መድረክ ባለፈ ለዓለም አቀፉ ንግድ እንደ ድልድይ ያገለግላል፡፡